
በአዶናዊሮስ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽንስ ክፍል ተዘጋጅቶ የሚቀርበው “መልክአ-ሃሳብ” የሬዲዮ ፕሮግራም ትኩረት ኢትዮጵያ ታላቅ በነበረችበት ወቅት ይኖሩ የነበሩ ታላቅ ሕዝቦች ይመሩበት በነበረው ረቂቅ ጥበባዊ እና ጥልቅ የሕይወት ፍልስፍና ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ በዚህም ረገድ ፕሮግራሙ ምልከታውን በወቅቱ የነበረውን የኢትዮጵያዊያን የአስተሳሰብ የከፍታ መጠንን ከቃል ባለፈ በሚታይ ተጨባጭ አስረጂዎች ሊያሳዩ በሚችሉ ቱባ ጥበባዊ አስተሳሰቦች ላይ አድርጓል፡፡የ “መልክአ-ሃሳብ” ሬዲዮ ፕሮግራም አላማ ነፃ የዕይታ አማራጮች እንዲሰፉ መደላደል በመፍጠርና ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሐሳቦችና ፍልስፍናዎች ላይ የተገነባ የአመለካከት ለውጥ እንዲፋጠን በማድረግ የራሱ ሐሳብና አቋም ያለው ትውልድ እንዲፈጠር አስተዋፅኦ ማድረግ ነው፡፡ ፕሮግራሙ በተለያዩ የጋራ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ያላቸውን ከፍ ያሉ ሃሳቦችን በማንሳት በሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ያሉ ተጨማሪ የዕይታ አቅጣጫዎችን ለማሳየትና አዲስ የማስተዋል አቅም ለመፍጠር ይሰራል፡፡ ይህንን በማድረግም ፕሮግራሙ ተከታታዮቹን ወደ አንድ የሐሳብ ከፍታ እንደሚያወጣ እናምናለን፡፡